“ዛሚ አልተሸጠም፤ በትብብር እየሠራን ነው” ጋዜጠኛ ሚሚ ስብሃቱ

ጋዜጠኛ ሚሚ ስብሃቱ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በቴአትር ጥበባት ተመርቀዋል። የኮሌጅ ተማሪ ሳሉ ጀምረው በሚዲያ ላይ መሳተፍ የጀመሩት ሚሚ፤ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን በትርፍ ጊዜ ይሠሩ ነበር። ከተመረቁ በኋላም የኢትዮጵያ ፊልም ኮርፖሬሽንን ተቀላቅለው ዘጋቢ ፊልሞችን ሠርተዋል።

የትምህርት እድል አግኝተው ወደ አሜሪካ፤ ኒዮርክ አቅንተዋል። በወቅቱ በአገሪቱ ውስጥ የነበረው የፖለቲካ ሁኔታ [ከደርግ መውደቅ በኋላ] ያላማራቸው ሚሚ፤ እዚያው ለመቆየት ወስነው በአሜሪካ ድምፅ የአማርኛው ፕሮግራም ተቀጥረው በጋዜጠኝነት ለበርካታ ዓመታት አገልግለዋል።

ከአሜሪካ ከተመለሱ በኋላም ዛሚ 90.7 ራዲዮ ጣቢያን አቋቁመው እየሠሩ ይገኛሉ። ይህ ራዲዮ ጣቢያ የተለያየ የፖለቲካ አቋም ባላቸው አካላት ትችቶች ሲዘነዘሩበት ቆይቷል። በተደጋጋሚ ሊዘጋ ነው የሚል ዜናም ተሰምቷል። አሁን ደግሞ በእጅ አዙር ተሸጧል፤ አልተሸጠም የሚሉ ውዝግቦች ይነሱበታል።

አዲስ ዓመትን አስመልክተን ከሚዲያ የራቁ ሰዎችን ስናፈላልግ ጋዜጠኛ ሚሚን አግኝተን ስለ ጣቢያውና ስለ ግል ሕይወታቸው ጠይቀናቸዋል።

አሁን የት ነው ያሉት?

አሜሪካን አገር ነው ያለሁት። Medical check up [የጤና ምርመራ] ላይ ነኝ በየዓመቱ የጤና ምርመራ አደርጋለሁ።

የጤንነት ሁኔታዎ እንዴት ነው?

በጣም ደህና ነኝ። በጣም በሚገርም ዓይነት ባለፈው ጊዜ ዐይኔን ቀዶ ሕክምና አድርጌ ነበር። የሚገርመው የምርመራ ውጤቴንም ተቀብያለሁ። በጥሩ ጤንነት ላይ ነው ያለሁት [ሳቅ] በዚህ እድሜ የሚመጡ ብዙ ነገሮች አሉ- በእኔ እድሜ። ስለዚህ ከዚያ አንፃር ሲታይ፣ እ. . ከሥራዬ ‘ስትረስ ፉል’ [ውጥረት መብዛት] አንፃር ሲታይ፤ እነዚህ አስፈሪ የሆኑት እንደ ስኳር፣ ግፊት ምናምን ያሉት የሉብኝም። በዚያ ተደስቻለሁ። የሚገርምሽ ስፖርት አልሠራም። ምን አልባት አመጋጋብ ሊሆን ይችላል።

አሁን በምን ሥራ ላይ ነው ያሉት?

አሁን ዛሚ ‘ሪ ብራንድ’ እየተደረገ ነው። እንደገና ደግሞ የ ‘ትሬኒንግ’ [ሥልጠና]፤ ጋዜጠኞችን በዘለቄታዊ የሥልጠና ተቋም የመገንባት ሥራ ላይ ነው ያለሁት። ብዙ ሥራዎች ላይ ነው ያለሁት፤ አሁን ሕክምና ላይ ብሆንም።

የማማከር ሥራዎችን ይሠራሉ ሲባል ሰማሁ። ማንን ነው የሚያማክሩት?

እሠራለሁ። ግን በአሁኑ ሰዓት ‘ሊስት’ ማድረግ [መዘርዘር] አልፈልግም። ብዙዎቹ ገና በተለያየ ደረጃ ላይ ስለሆኑ እሱን አሁን ‘ሊስት’ ማድረጉ [መዘርዘሩ] ጥሩ አይሆንም። ገና ነው። a little bit early፤ ግን ሥራ አልፈታሁም ለማለት ነው [ሳቅ]።

ዛሚ ራዲዮ ጣቢያን ‘ተሸጧል’ እየተባለ ይወራል። እውነት ነው?

ዛሚ ብዙ ጊዜ የአየር ሰዓት ወስደው የሚሰሩ ‘ፓርትነርስ’ [አጋር ድርጅቶች] አሉት። በተለያየ መንገድ አብረውን የሚሠሩ በርካታ ድርጅቶች አሉ። ስለዚህ ከብዙ ሰዎች ጋር እንሠራለን።

ዛሚ የሚዲያ ተቋም እንደመሆኑ መርሁን እና ሥነ ምግባሩን ከሚያከብሩ፣ አላማው ለሕዝብ አገልግሎት የሚሰጥ ተቋም እንደመሆኑ ያንን ማድረግ ከሚፈልጉ፣ መሠረታዊ በሆኑት የጋዜጠኞች መስፈርቶች ዙሪያ ከሚንቀሳቀሱ፣ ከሁሉ በላይ ደግሞ ለህብረተሰባችን አገልግሎት ከሚሰጡ፣ መስጠት ከሚፈልጉ፣ ከማናቸውም ወገኖች ጋር በትብብር እንሠራለን። ስለዚህ ‘ሪ ብራንድ’ እያደረግን [እንደገና እያደራጀን] ነው።

ሌሎች ጣቢያዎችም እኮ እንደዚህ ያደርጋሉ። ለምን በዛሚ ላይ ትንሽ ለየት እንደሚል ባይገባኝም፤ በትብብር እንሠራለን- ከተለያዩ ወገኖች ጋር።

የአየር ሰዓት መስጠት የተለመደ ነው። ስለዚህ ‘በትብብር’ ሲሉኝ የአክሲዎን ሽያጭ ነው ማለት ነው? ትብብር ሲሉ ግልፅ ቢያደርጉልኝ?

የአክሲዎን ሽያጭ አይደለም። በትብብር የሚሠራባቸው ብዙ ዓይነት መንገዶች አሉ። እነዚህን ደረጃ በደረጃ በቢዝነስ ‘ዲፓርትመንቱ’ [ክፍሉ] ነው የሚሠሩት። ይህ ደግሞ በቀጥታ የሚመለከተው አቶ ዘሪሁን ተሾመን [ባለቤታቸው] ነው። እኔን የፕሮግራም፣ የሙያው ጉዳይ ነው የሚመለከተኝ።

ከዚህ ቀደምም የምሠራው በዚያው መስመር ነው። ነገር ግን በ’ሪ ብራንዲንጉ’ ሂደት ውስጥ፤ በርካታ ለውጦች. . . አዳዲስ ፕሮግራሞች፣ አዳዲስ አጋሮች እ. . . አሰባስበን እንግዲህ ተጀምሯል።

ከማን ጋር ነው በትብብር እየሠራችሁ ያላችሁት?

ከተለያየ አካላት ጋር። በርካታ ናቸው።

ለተለያዩ መገናኛ ብዙኃን ሥልጠናዎችን ይሰጡ እንደነበር አውቃለሁ። እስካሁን ለምን ያህል የሚዲያ ባለሙያዎች ሥልጠና ሰጡ?

በጣም ብዙ ነው። ገና ዛሚ ሳይቋቋም በነበሩት ሁለት ዓመታት በየክልሉ እየዞርኩ ሳሰልጥን ነበር። ከዚያ ይጀምራል እንግዲህ። በጣም ብዙ ነው።

በጊዜው አገልግሎት ላይ ለነበሩ መገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች፣ ለማህበረሰብ ራዲዮ በጎ ፈቃደኛ ባለሙያዎች፣ አዲስ ለተቋቋሙ መገናኛ ብዙሃን ከዚያ ደግሞ በዛሚ ሥር በየዓመቱ ሥልጠናዎችን እሰጥ ነበር። ቁጥሩን ግን በፍፁም አላውቀውም። ግን ከ300 በላይ ይሆናል። አሁንም ይሄንን ሥልጠና በደንብ በተደራጀ መልኩ ለማድረግ አስበናል።

በትርፍ ጊዜዎ ምንድን ነው የሚያደርጉት?

ብዙ ጊዜ መዝናኛ የምለው ፊልም እና መጽሐፍ ነው። ጊዜ ካገኘሁ እነዚህ ሁለቱ ላይ ነው ጊዜየን የማሳልፈው። አሁን ለጊዜው እንግሊዝኛ መጻሕፍት ናቸው እያነበብኳቸው ያለሁት። Sapiens [ሳፒያንስ] በተከታታይ የወጣ ሁለት መጽሐፍ አለ። አንዱን ጨርሼ አንዱ ላይ ነው ያለሁት።

የማንን ሙዚቃ ይወዳሉ?

እ . . . ይለያያል። አዳዲስ ዘፈኖች በጣም እከታተላለሁ። ወጣቶቹ ደስ ይሉኛል። ባህላዊ የሆኑ ዘፈኖችን እሰማለሁ፤ አያለሁ።

ወደፊት ምንድን ነው እቅድዎት?

መጽሐፍ ለመጻፍ እቅድ አለኝ። ‘ሻዶው ራይተር’ [ጸሐፊ] እየፈለኩ ነው። ‘ስኬለተን’ [አፅመ ታሪኩ] ወጥቷል። ጎበዝ ፀሐፊ እየፈለኩ ነው። ያው ቁጭ ብዬ መጻፍ ስለማልችል፤ ሥራ ላይም ስለሆንኩኝ እ. . . የሚያግዝ ጸሐፊ ባገኝ ይበልጥ ይፋጠናል ብየ አስባለሁ።

መጽፉ በምን ላይ የሚያተኩር ነው?

ሙያዬ ከግለ ታሪኬ ጋር በጣም የተያያዘ ስለሆነ ሁለቱንም ‘ኮምባይን’ ያደረገ [ያካተተ] ለሌሎችም ትምህርት ሊሆን የሚችል የሕይወት ምዕራፌን አጋራለሁ ብዬ አስባለሁ።

የግል ሕይወትዎስ?

በትዳር 25 ዓመት ቆይቻለሁ። ሩብ ምዕተ ዓመት [ሳቅ] ሁለት ልጆች አሉኝ። አንዱ ትልቅ ነው። አሜሪካ ነው የሚኖረው። አብራኝ ያለችው ደግሞ ዘጠኝ ዓመቷ ነው። በጣም ደስተኛ ነኝ። በግል ሕይወቴ ደስተኛ የሆንኩት፤ በቤቴ በጣም ‘ሰፖርቲቭ’ [ደጋፊ] የሆነ ቤተሰብ ስላለኝ ነው። በጣም ‘ቻሌንጂንግ’ [ተግዳሮት የበዛበት] ቢሆንም፤ እስከዛሬ ድረስ ያለሁትም በዚያ ምክንያት ነው። ትልቁ ድጋፌ ያ ነው።

በሥራዬ ተግዳሮት አለብኝ ብለውኛል። የፈተነዎት ምንድን ነው?

ብዙ ነገሮች አሉ። [ሳቅ] ብዙ ተግዳሮቶች አሉ። የሚጠበቁ፣ የማይጠበቁ፣ ድንገት የሚመጡ ‘ቻሌንጅስ’ [ተግዳሮቶች] አሉ። ብዙ ናቸው። በተለይ እንደኛ ዓይነት ሙያ ውስጥ በምትኖሪ ጊዜ፤ አንችም ታውቂዋለሽ፤ ብዙ ፈተናዎች አሉ። ይሄ ነው፤ ይሄ ነው አልልም። ሙያችን አልጋ ባልጋ የሆነ ሙያ አይደለም። ስለዚህ ብዙ ፈተናዎችና ችግሮች አሉበት።

ጋዜጠኛ ሚሚ ስብሃቱ ከጋዜጠና መዓዛ ብሩ ጋር በስተግራ አቶ አማረ አረጋዊ ይታያሉ

ዛሚ በእጅ አዙር ተሸጧል?

ዛሚ 90.7ን በተመለከተ በተለያዩ ጊዜ የተለያዩ መረጃዎች ይወጣሉ። ከዚህ ቀደም ሊዘጋ ነው ተብሎ የራዲዮ ጣቢያው ባለቤትና ዋና ሥራ አስፈፃሚ ከሆኑት አቶ ዘሪሁን ተሾመ ጋር ቃለ ምልልስ ማድረጋችን ይታወሳል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ በተለያዩ ማኅበራዊ ሚዲያዎች ዛሚ 90.7 በነበረበት ቁመና አይቀጥልም፤ በእጅ አዙር ተሸጧል የሚሉ ወሬዎች ይናፈሳሉ።

ወሬው የገዥውን ስም እስከመጥቀስ የደረሰም ነበር። ከወ/ሮ ሚሚ ጋር ቃለ ምልልስ ስናደርግ፤ እንዲህ ዓይነት ጉዳዮችን የሚመለከተው የጣቢያው ባለቤትና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ዘሪሁን ተሾመ [ባለቤታቸው] ነው ስላሉን ወደ እርሳቸው ደውለን ነበር።

ዛሚ ተሸጧል?

አልተሸጠም! ስሙን ለውጠነዋል። አመራር ቀይረናል። አዳዲስ ፕሮግራሞች አምጥተናል። ፉክክሩ እየበረታ ነው። ይህንን ካጠናከርን በኋላ ደግሞ ፍላጎት ላለው የተወሰነ አክሲዮን ለመሸጥ አቅጣጫ ይዘናል።

ስሙን መለወጥ ለምን አስፈለገ?

እንደምታውቂው አገራችን ላይ ፍረጃ ምናምኖች አሉ- አንደኛው እሱ ነው። ሁለተኛው ምክንያት ዛሚ የሚለው ስያሜ በዋነኛነት የሚወክለው የሁለት ግለሰቦችን ስም የመጀመሪያ ፊደል ነው [የእኔና የባለቤቴን]። አሁን ያስቀመጥነው አቅጣጫ ደግሞ፤ ሌሎች ፍላጎት ያላቸው ሁለት ያህል የአክሲዎን ባለድርሻ አካላት እንዲገቡ እንፈልጋለን።

ፍረጃ ሲሉኝ?

ከአንድ ፖለቲካ ወገን ጋር ማያያዝ ወ.ዘ. ተ። ስለሆነም ያንን ጥላም ለመግፈፍ ነው። በዋናነት ግን ለሁሉም አስማሚ የሆነ፤ በእናንተ ስም ብቻ ነው የማይባል፤ ወደፊት ያቀድነው ከተሳካ እና የሚመጡ የአክሲዎን ባለድርሻዎች ከኖሩ እነሱንም ለማበረታታት ጭምር ነው።

ስሙ ከዛሚ ወደ አዋሽ ነው የተለወጠው። ስያሜውን እንዴት አገኘ?

እኔ ነኝ ያወጣሁለት። አዋሽን የመረጥንበት የራሱ መነሻ አለው። አዋሽ ብቸኛው ኢትዮጵያዊ ወንዝ ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ ነው የሚያበቃው። ስለዚህ በዚህ ደረጃ ካየሽው ታማኝ ማለት ነው። ከአገሩ የማይወጣ፤ ላገሩ የሆነ።

ሌላው አዋሽ ጥልቅ [Gorge] ሸለቆ ውስጥ የሚፈስ በመሆኑ ነው። በሌላ በኩል ጉራጌን፣ ደቡብን፣ ኦሮሚያን፣ የተወሰነ የአፋር ቦታ፣ ሶማሌን፣ እንዲሁም የአማራን የተወሰነ ቦታ ይነካል። በመሆኑም ታማኝ፣ ጥልቅ፣ ሕብረ ብሔራዊ ወይም አስተሳሳሪ ማለት ነው።

ስለዚህ ጣቢያው ላይ ሲተላለፉ የነበሩ የፕሮግራሞች ቅርፅና ይዘት ተለውጧል?

ተለውጠዋል። አዳዲስ አጋር ድርጅቶች ገብተዋል። የመዝናኛ ፕሮግራሞች በርከት ብለዋል። ‘የጋዜጠኞች ክብ ጠረጴዛ’ በአዲስ ‘ፎርማት’ [ቅርፅ]፣ በአዲስ ሰዎች ይጀምራል።

‘የጋዜጠኞች ክብ ጠረጴዛ’ ፕሮግራም በማን ይመራል ማለት ነው?

ገና ሰው አልመደብንለትም፤ ግን አዲስ ዳይሬክተር ሾመናል። እሱም ሊመራው ይችላል። ታዋቂ ሰዎችም እየተሳተፉበት የጦፈ የክርክር መድረክ ሆኖ ነው የሚቀጥለው።

ጋዜጠኛ ሚሚስ?

ወ/ሮ ሚሚ ለጊዜው ሥልጠና እና ማማከር ላይ ነው ያለችው። የሥልጠናውን ዘርፍ የያዘችልን እሷ ነች። ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ግን እሷም መመለስ ትችላለች።

ስለዚህ እስካሁን አብሯችሁ የሚሠራ አካል የለም?

መቶ ፐርሰንት። በነገርሽ ላይ በኢትዮጵያ ሕግ መሠረት ራዲዮ ጣቢያ መሸጥ አይቻልም። ስለዚህ በእርግጠኝነት የምነግርሽ እስካሁን ድረስ የሞከርነው ከናሁ ቴሌቪዥን ጋር ነበር። ከእነርሱ ጋር አልተግባባንም፤ ስላልተግባባን የደረስነው ስምምነት እንዲፈርስ አድርገን፤ አሁን በግልግል ዳኝነት ላይ ነን።

በምንድን ነው ያልተግባባችሁት?

በአከፋፈል ሒደት. . . ምናምን ወዘተረፈ። ግልግል ላይ ያለ ነገር ስለሆነ I can not go to the details [ወደ ዝርዝሩ ልገባ አልችልም]። ግን የግልግል ዳኝነት ላይ ነን።

አብረዋችሁ ሊሠሩ የሚችሉት እነማን እንደሆኑ ይታወቃሉ? ድርጅትም ከሆነ?

አይታወቁም። ግን እስከ ሁለት ነው የሚሆነው። እስካሁን ድረስ በግል ያነጋገርነው አካል የለም፤ ግን ለማድረግ እየሞከርን ነው። ፍላጎት ያላቸው ሰዎች ይኖራሉ ብለን እንገምታለን።

Leave a Reply

%d bloggers like this:
SPONSORSHIP BENEFITS