የፀጥታ መደፍረስ በተከሰተባቸው በኦሮሚያ፣ ሀረርና ድሬዳዋ አካባቢዎች የመከላከያ ሰራዊት የማረጋጋት ስራ እያከናወነ ነው

የመከላከያ ሰራዊት የፀጥታ መደፍረስ በተከሰተባቸው የኦሮሚያ ክልል ፣ ሀረር እና ድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር አካባቢዎች ከአባ ገዳዎች፣ ከሃይማኖት መሪዎች፣ ወጣቶች እና ከህብረተሰቡ ጋር በመሆን የማረጋጋት ስራ እያከናወነ መሆኑን አስታወቀ፡፡

የክልሉ መንግስት ያቀረበውን ጥያቄ ተከትሎ ሰራዊቱ የፀጥታ ችግር በተከሰተባቸው በተለይም በአምቦ፣ ቢሾፍቱ፣ ባሌ ሮቢ፣ አዳማ፣ ሞጆ እንዲሁም በድሬዳዋ እና ሀረር መሰማራቱን ሚኒስቴሩ አስታውቋል። በዛሬው ዕለት በሰጠው መግለጫም በእነዚህ አካባቢዎች ከኦሮሚያ ክልል እና ከድሬዳዋ ከተማ አስተዳር የፀጥታ አካላት፣ ከአካባቢው ነዋሪዎች፣ ወጣቶች እና አባገዳዎች ጋር በመሆን ችግሮችን የማስቆም ስራ እየተከናወነ መሆኑን የመከላከያ ኢንዶክትሪኔሽንና የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተሩ ሜጄር ጄኔራል መሀመድ ተሰማ ተናግረዋል፡፡ ይህን ተከትሎም የተዘጉ መንገዶችን የማስከፈት ስራ እየተከናወነ የሚገኘ ሲሆን የንግድ ተቋማትም ወደ ስራ እየተመለሱ እንደሚገኝ ተነግሯል፡፡ በተሰራው ስራ ተጨማሪ የሰው ህይወት እና ንብረት ከጥፋት ማትረፍ የተቻለ ቢሆንም መከላከያ ሰራዊት በፍጥነት ባልደረሰባቸው አካባቢዎች ጉዳት ማጋጠሙን ጠቁመዋል። ሰላምን በታጠቀ ሀይል ብቻ ማረጋጋት አይቻልም ያሉት ሜጄር ጄኔራል መሀመድ ሰላምን ለማስፈን የህብረተሰቡ ሚና ከፍ ያለ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ የፀጥታ መደፍረስ ያጋጠማቸው አካባቢዎች ወደ ቀደመ ሰላማቸው እስከሚመለሱ ድረስ የሀገር መከላከያ ሰራዊት አካባቢዎቹን የማረጋጋቱን ስራ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል፡፡ ህብረተሰቡም እያደረገ ያለውን ተሳትፎ አጠናክሮ እንደቂጥልም ጥሪ አቅርበዋል።

Leave a Reply

%d bloggers like this:
SPONSORSHIP BENEFITS