5 ሚሊየን ብር ግምት ያላቸው በህገ ወጥ መንገድ ወደ ሀገር የገቡ ዕቃዎች ተያዙ

በሁለት ወራት ውስጥ በግል መገልገያ ሽፋን የገቡ 5 ሚሊየን ብር ግምት ያላቸው ዕቃዎች መያዛቸውን የገቢዎች ሚስቴር አስታወቀ፡፡

የአዲስ አበባ ቃሊቲ ጉምሩክ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት የወጪ ንግድ ያልሆኑ ገቢ ዕቃዎች አወጣጥ የስራ ሂደት አስተባባሪ አቶ ሙሌ አብዲሳ፥ ባለፉት ሁለት ወራት ከ5 ሚሊየን ብር በላይ የሚገመቱ ሸቀጦች ቀረጥ ሳይከፈልባቸው በህገወጥ መንገድ ለመግባት ሲሞክሩ መያዛቸውን ገልፀዋል፡፡

እቃዎቹ ከስደት ተመላሽ ኢትዮጵያውያንን ለመደገፍ የወጣውን መመሪያ ቁጥር 51/2011 ሽፋን በማድረግ በህገ ወጥ መንገድ ወደ ሀገር ቤት የገቡ የመገልገያ እቃዎች መሆናቸውን ነው የተናገሩት፡፡

ከስደት ተመላሽ ዜጎች መገልገያ ዕቃዎቻቸውን ቀረጥ ሳይከፍሉ ሲያስገቡ አገልግሎቱን የበለጠ የተሳለጠ ለማድረግ ከቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ በተጨማሪ በየብስ እንዲያስገቡ መደረጉንም አስታውሰዋል፡፡

ከላይ የተጠቀሰው መመሪያ የዕቃዎችን አይነትና መጠን በግልፅ ያላስቀመጠ መሆኑንም አስተባባሪው ተናግረዋል።

በዚህም ህገ ወጥ ነጋዴዎቹ ይህንን ክፍተት በመጠቀም ከስደት ተመላሾች ጋር በመመሳጠር ለንግድ አገልግሎት የሚውሉ እቃዎችን እያስገቡ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

እቃዎቹ መነሻቸውን ከመካከለኛው ምስራቅ ሀገራት ያደረጉ መገልገያ ቁሳቁሶች ናቸው።

በዚህ ረገድ እየተስተዋለ ያለውን ዝርፊያ ለማስቆም ቆንፅላ ጽህፈት ቤቶች ከጉምሩክ ኮሚሽን ትክክለኛውን መረጃ ወስደው በውጭ ሃገራት ላሉ ዜጎች ግንዛቤ የመፍጠር እና ህጉን ፈትሾ ክፍተቶችን የማረም ስራ ቢሰራ ችግሩን ለመቅረፍ ያግዛል ብለዋል፡፡

ወደፊት ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት የሚያደርገውን ቁጥጥር አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ከገኒዎች ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

Leave a Reply

%d bloggers like this:
SPONSORSHIP BENEFITS